የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል! - ሪፖርተር - Ethiopian Reporter - #1 Best And Reliable News Source In Ethiopia
Saturday, June 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ ላይ ማተኮር እየበዛ ለመግለጽ የሚያዳግቱ ጥፋቶች በዝተዋል፡፡ ጥፋቶቹ የንፁኃንን ሕይወት የሚያስገብሩ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የሚያፈናቅሉና የደሃ አገር ሀብት የሚያወድሙ ግጭቶችን እያመረቱ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአገሪቱ የፖለቲካም ሆነ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ልሂቃን፣ ለአገር ዘለቄታዊ ሰላም የሚያስገኙ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ዳተኝነት እያሳዩ መሆናቸው ችግሮቹን እያከበዳቸው ነው፡፡ ዳር ከሚይዙት በተጨማሪ ለሰላም መስፈን ጥረት ከማድረግ ይልቅ ነዳጅና ክብሪት ይዘው የሚዞሩ መብዛታቸው ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካው ጡዘት እያስደነበራቸው ከፖለቲካው ምኩራብ የሚሸሹ መበርከታቸውም ያሳስባል፡፡ ልሂቃኑ ግራ አጋቢ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የመነጋገሪያ መድረክ መፍጠር አዳጋች ነው፡፡

ይሁንና ‹‹ሕልም አለ ተብሎ ሳይተኛ አይታደርም›› እንደሚባለው ችግሮቹን ከመጋፈጥ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አገር በትውልዶች ቅብብል እዚህ ትውልድ እጅ እስክትደርስ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ኢትዮጵያን አንበርክከው በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ከዘመቱ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ጀምሮ፣ በየዘመናቱ የተነሱ ኃያላንን ለመመከት በርካታ ትውልዶች በታሪክ በደማቁ የተመዘገቡ ታላላቅ መስዋዕትነቶችን ከፍለው አገራቸውን አስከብረዋል፡፡ በትውልዶች ቅብብል እዚህ የደረሰችውን ኢትዮጵያን ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድም ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ይህንን ክቡር ዓላማ ለማስፈጸም ግን በአገር ህልውና ላይ መደራደርም ሆነ መቆመር አይፈቀድም፡፡ የጥንቶቹ ልዩነቶቻቸውን አደብ አስገዝተው የውጭ ጠላቶችን እንደ መከቱት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ትውልድም ልዩነቶቹን ፈር ማስያዝ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመነጋገርና ከመደራደር የሚቀድም አማራጭ እንደሌለ ይታወቅ፡፡

ለንግግርና ለድርድር ዝግጁ ለመሆን ግን ከመንግሥት ጀምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መከባበር፣ ዕውቅና መሰጣጠትና በእኩልነት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ቁርጠኛ መሆናቸውን በተግባር ማስመስከር አለባቸው፡፡ ልዩነትን እያጎኑና አሉታዊ ስም እየተለጣጠፉ ግጭትን ማጦዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ ጤና፣ ትምህርትና ዕድገት አያስገኝም፡፡ እርስ በርስ ‹ፀረ ሰላም ኃይል›፣ ‹አሸባሪ›፣ ‹ፋሽስት› እና መሰል የጥላቻ ቅጽሎችን ስያሜ ላይ በመለጠፍ የሚደረገው የጥፋት ጉዞ መገታት አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመግፋት፣ ወደ ለየለት አምባገነንነት የሚያስገቡ ቅራኔዎች ላይ ማተኮር ግጭቶችን ከመፈልፈል የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከእነዚህ አላስፈላጊና ጥፋት አባባሽ ሐሳቦችና ድርጊቶች ገለል በማለት፣ ለጋራ አገር ልማትና ዕድገት በአንድነት ሊያቆሙ የሚያስችሉ አማራጮች ቅድሚያ መስጠት የግድ መሆን አለበት፡፡

ወርኃ የካቲት ከባተ ጀምሮ እስካሁን በተለያዩ መድረኮች በልዩ ልዩ ሁነቶች ሲዘከር የነበረው የ1966 ዓ.ም. አብዮት፣ ለዚህ ትውልድ ትልቅ የመማሪያ ሰሌዳ መሆን ነበረበት፡፡ የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውጤት የሆነው አብዮት ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል አስደሳች መፈክር ተጀምሮ፣ እስካሁን ብዙዎችን በሚያስቆጭ ሁኔታ በደም ተጨማልቆ ማለፉ የዚያ ትውልድ የልብ ስብራት ነበር፡፡ በወቅቱ መስከንና ግራና ቀኙን በአርቆ አሳቢነት መቃኘት ባለመቻሉ ብቻ አንድ ትውልድ ለግድያ፣ ለእስራት፣ ለሥቃይና ለስደት ተዳርጎ አገሪቱ ከል ለብሳ ነበር፡፡ በተለይ በቀይና በነጭ ሽብሮች ወንድማማቾችና እህትማማቾች ጎራ ለይተው መፋጀታቸው፣ እስካሁን የማይሽር ቁስል ሆኖ ዘልቋል፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መከታና አርዓያ የሆኑት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የልጅ ልጆች፣ በርዕዮተ ዓለማዊ የመስመር ልዩነት መፋጀታቸው የታሪክ የእግር እሳት ነው፡፡

ያንን ከመሰለ ዘግናኝና አስደንጋጭ የጥፋት ታሪክ መማር ባለመፈለጉ ወይም በዳተኝነት ሳቢያ፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላው እየተሸጋገረች የቀውስ የስበት ማዕከል ሆና ቀጥላለች፡፡ በዘመነ ደርግ 17 ዓመታት የተካሄዱ ጦርነቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ጠፍቶ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩት ደግሞ አካላቸው ጎድሎ፣ የአገር ኢኮኖሚ እሳት ውስጥ እንደተጣለ ፕላስቲክ በጦርነቱ ተቃጥሎና ተኮማትሮ፣ በዘመኑ የነበሩ ወጣቶች የመማርና የማደግ ተስፋ ደብዝዞ ለጦርነት ሲማገዱ ቆይተው ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲቆናጠጥ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡ ኤርትራ ተገንጥላ ብዙም ሳይቆይ ለሁለት ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል በተካሄደ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖች ረገፉ፡፡ ኢሕአዴግ የሚቃወሙትን በሙሉ ማሰር፣ ማሳደድና መግደል መደበኛ ሥራው ሆኖ በአገሪቱ ሰቆቃ ሰፈነ፡፡ ሰቆቃው ግድቡን ጥሶ በተነሳው ሕዝባዊ ማዕበል ተገፍትሮ ለመጣል በቃ፡፡

ኢሕአዴግ ከተወገደ በኋላ መላ አገሪቱ በለውጥ ማዕበል ተጥለቅልቃ በርካታ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መታየት ጀመሩ፡፡ እነዚህ ጅምሮች ግን ወዲያው ነበር በየአካባቢው ራሳቸውን ከሕግ በላይ ባደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መሪነት ግድያዎችና ማፈናቀሎች የደበዘዙት፡፡ ለውጡን በጋራ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈኛ ለማድረግ የነበረው ተስፋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ነውረኛ ጭካኔዎች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት፣ በአብዛኛው በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ሲገታ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተጠናክሮ በመቀጠሉ ደበዘዘ፡፡ ካለፉት ስህተቶች መማር ባለመቻሉ አገር እየደማች ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡ ይህንን የጥፋት ጉዞ ተባብሮ ማስቆም ይገባል፡፡ የአገሪቱ ልሂቃን ከሴራና ከቁዘማ ተላቃችሁ ከጥፋት ውስጥ የመውጫ መፍትሔ ፈልጉ፡፡ የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...

እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

በአሰፋ አደፍርስ ኢትዮጵያውያን ከየትም እንምጣ ከየት እስከ 1445 ዓ.ም. እስላማዊና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ይዋል!

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዲጂታል ሪፎርም ሥራን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ የፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ዓመታት...

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...